Welcome
Login / Register
Loading...

Ethiopia: Erso Behonu Men Yadergalu Radio Program | FanaBC

እርሶ ቢሆኑ ምን ያደርጋሉ?

ትምህርት ቤት ከተዋወኳት ባለቤቴ ጋር በይፋ በጋብቻ ከመተሳሰራችን በፊት ብዙ ጊዜ በአብሮነት አሳልፈናል ከዚያም በሁለታችንም ቤተሰቦች መልካም ፈቃድ በ1997 ዓ.ም. ጋብቻ ፈጸምን።

ስራየ ሹፍርና ሲሆን ባለቤቴ ደግሞ የቤት እመቤት ናት፤ በትዳራችን ሁለት የ8 እና የ6 አመት ልጆች አፍርተናል፤ ከልጆቼ እና ባለቤቴ ጋር ጊዜ የማሳልፈው በበዓላትና አንዳንድ ጊዜ ብቻ ነው፤ ይሁን እንጅ ኑሯችን ሰላም፣ ፍቅር እና መተሳሰብ የሞላበት ነበር።

የዛሬ ሶስት አመት ሱዳን ሃገር ትኖር የነበረች የባለቤቴ እህት በእንግድነት ወደ ቤታችን መጣች፤ በወቅቱ በስራ ምክንያት እኔ ቤት አልነበርኩም፤ ከስራ ወደ ቤት በተመለስኩበት አጋጣሚ ግን የባለቤቴ ሁኔታ እንደቀድሞው አልነበረም እጅግ ተለዋወጠችብኝ።

"አንተ ምኔ ነህ? ባለቤቴ ወይስ?" ብላ ያልጠበኩትን ነገር ተናገረችኝ፤ በሁኔታው ደነገጥኩ እህቷ ምን እንዳለቻትም አላውቅም። ከዚያም ኑሯችንን ለማሻሻል መስራትና ለልጆቻችን ቅርስ መተው እንዳለብኝ አስረድቻት ተግባባን እና ጥሩ ጊዜ አሳልፈን ወደ ስራየ ተመለስኩ።

ይህ ከሆነ ከአንድ አመት በኋላም እህቷ በድጋሚ ወደ ቤታችን መጣች እኔም በአጋጣሚ ለስራ ወጣሁ፤ ለስራ ከወጣሁ በኋላ ስልክ በተደጋጋሚ ብደውልም አታነሳም ከቀናት በኋላ መታመሟ ተነግሮኝ ወደ ቤት በመመለስ ካሳከምኳት በኋላ ለስራ ተመልሸ ወጣሁ፤ እየተመላለስኩም አስታመምኳት። በወቅቱ ግን ከጭንቀት ውጭ ምንም በሽታ አልነበረባትም እኔም አረጋግችያት በድጋሚ ወደ ስራየ ተመለስኩ።

ከቀናት በኋላም ተመልሸ አዲስ አመት በጥሩ ሁኔታ አብረን አክብረንና 15 ቀናት ቆይቼ ወደ ስራየ ሄድኩ፤ ከሳምንት በኋላ ግን ያልጠበኩትን ነገር ሰማሁ፤ ስልክ ተደውሎ ባለቤቴ ልጆቹንና ቤቱን ጥላ መሄዷ ተነገረኝና በጣም ደነገጥኩ፤ ወደ ልጆቼም ተመለስኩ።

ልጆቼን ለቤተሰቦቼ ሰጥቼ ባለቤቴን ማፈላለግ ጀመርኩ ላገኛት ግን አልቻልኩም፤ ትሄዳለች ብዬ የምጠረጥረው ቦታ ሁሉ ፈለኳት አላገኘኋትም ቤተሰቦቿም ሊያግዙኝ ፈቃደኛ አልሆኑም። በመጨረሻም ልጆቼን ለቤተሰቦቸ ሰጥቼ ጉዳዩን ለፖሊስ አሳውቄ ወደ ስራየ ተመለስኩ።

ቤተሰቦቼም ጫና ስለበዛባቸው ልጆቼን ከእነርሱ ጥቂት በእድሜ ከፍ ለምትል የአክስቴ ልጅ አደራ ሰጧት፤ እርሷም ከትምህርቷ ጎን ለጎን ልጆቼን የመንከባከቡን ሃላፊነት ተረከበች።

ከጥቂት ጊዜ በኋላ ባለቤቴ ልጆቼ ጋር እየደወለች ናፍቃችሁኛል እንዳልመጣ ግን አባታችሁ ብር ከለከለኝ ማለት ጀመረች፤ በደወለችበት ስልክ መልሼ ስደውል ሱቅ መሆኑ ተነገረኝ፤ ባለቤቴም በተደጋጋሚ እንደዚህ ማድረጓን ቀጠለች።

ጉዳዩን ለማጣራት ያደረኩት ጥረት ግን እርሷ የምትጠቀመው የተለያየ ስልክ እና ቦታ ስለሆነ ሊሳካልኝ አልቻለም፤ ልጆቼ መረዳት የሚችሉበት ዕድሜ ላይ አይደሉምና እንዴት ላስረዳቸው?

ከባለቤቴም ጋር በግልፅ ስላላወራን ትመለሳለች ብየ ብዙ ብጠብቅም ጭራሽ ልጆቼ እንዲጠሉኝ እያደረገች ነው፤ ልጆቼም የእናትና አባት ፍቅር እያገኙ አይደለም፤ ሌላ ባገባ እኔ ብዙ ጊዜ ለስራ ስለምወጣ ልጆቼ በእንጀራ እናት እንዴት ይሆናሉ ብዬ እጨነቃለሁ።

ባሉበት እንዳይኖሩ ደግሞ የእርሷ ድርጊት ያስፈራኛል፤ አዕምሯቸውን እንዳታበላሽብኝም እሰጋለሁ።

የአክስቴ ልጅም በልጀነቷ ሃላፊነት መሸከሟ እየከበደኝና ሁኔታዋም እያሳዘነኝ ነው፤ ምን ባደርግ ይሻለኛል?

እርሶ ቢሆኑ ምን ያደርጋሉ?

Post your comment

Sign in or sign up to post comments.

Comments

Be the first to comment

Related Articles

RSS